ስለ እኛ

ዓለምጸሐይ ሺፈራው የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የቦሌ ክፍለ ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት አሥራ አንድ ክፍለ ከተሞች አንዱ ነው። ክፍለ ከተማው የአዲስ አበባችን ዓለም አቀፋዊ በር፣ የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው ብሔራዊ አየር መንገዳችንን ጨምሮ የበርካታ ታላላቅ ተቋማት መቀመጫ፣ ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የሚገኙበት፣ የከተማችን የዘመናዊነት ማሳያ እና ኅብራዊነት ደምቆ የሚታይበት ነው። 6,371 ሄክታር የቆዳ ስፋት ያለው የቦሌ ክፍለ ከተማ በአሥራ አንድ ወረዳዎች የተዋቀረ ሲሆን፣ የነዋሪው ሕዝብ ብዛት 308,995 ነው። የክፍለ ከተማችን አስተዳደር ለነዋሪው ኅብረተሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት በማሻሻልና በማዘመን የሕዝብን እርካታ ለማሳደግ በየደረጃው በትጋት እየሠራ ሲሆን፣ በክፍለ ከተማችን በምታገኙት አገልግሎት እርካታችሁን ከፍ ለማድረግ በርትተን የምንሠራ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ችግር ፈቺ በሆነ መንገድ ለማከናወንና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክፍተኛ ደረጃ እየሠራ ይገኛል። አስተዳደራችን ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ሰው ተኮር ተግባራትን በማከናወን በልዩ ልዩ መስኮች ተጠቃሚነትና ውጤታማነት የተረጋገጠበት ክፍለ ከተማ ለመሆን እያደረገ ባለው ጥረት የሚታዩና ተጨባጭ የሆኑ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ቦሌ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለያየ ደራጃ የሚኖሩበት ክፍለ ከተማ ነው። በመሆኑም ሁሉንም ኅብረተሰብ ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት በአሥራ አንዱም ወረዳዎቻችንና በክፍለ ከተማችን ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ በማድረግ፣ ቢሮዎችን በማዘመንና ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዘመነ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፈጻሚውና በአመራሩ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ክፍለ ከተማችን ከፍተኛ ስኬት ለማስመዝገብ ችሏል። በእነዚህ ተግባራትም ከዚህ ቀደም የሕዝብ ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምንጭ የነበሩ ተቋማትና አሠራሮች ተጨባጭ ለውጥ በማምጣታቸው የሕዝባችን እርካታም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል።

በክፍለ ከተማችን ለዓመታት የሕዝብ ጥያቄ የሆኑ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት አስተዳደራችን ሰፊ ሥራ አከናውኗል። የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በካፒታል በጀትና በአጋር አካላት ድጋፍ ገንብቶ ለአገልግሎት ያበቃው የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር፣ የሕዝብን ጥያቄዎች በተግባር በመመለስ ካስመዘገበው ስኬት ባሻገር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ውጤታማ የመሆን ተመክሮውንም በላቀ ደረጃ አሳድጓል። ለዚህ ስኬታችን መላው አመራር፣ ፈጻሚ ባለሙያዎች፣ አጋሮቻችን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የክፍለ ከተማችን ሕዝብ የጋራ ርብርብ ከፍተኛ ሚና አለው።

በክፍለ ከተማችን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን ከችግራቸው ወጥተው የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሰው ተኮር ተግባራትን በስፋት አከናውኗል። የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስና መልሶ በመገንባት፣ በማዕድ ማጋራት፣ እና በሌሎችሰው ተኮር ሥራዎቻችን ክፍለ ከተማችን ውጤታማ ከመሆኑ ባለፈ የበርካታ ወገኖችን እንባ በማበስ ለተሻለ ሕይወት ማብቃት ችሏል። እስካሁን ባከናወንናቸውና እያከናወንናቸው ባሉ ሥራዎቻችን በሀብታቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው ድጋፍ ላደረጉልን ባለሀብቶችና ተቋማት ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው። የቦሌ ክፍለ ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የከተማ ግብርና ከሚካሄድባቸው ክፍለ ከተሞች አንደኛውና ስኬታማው ክፍለ ከተማ ነው። በክፍለ ከተማው የሚኖሩ አርሶ አደሮች የመሬታቸውና የምርታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስተዳደራችን ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ዛሬ ላይ ክፍለ ከተማችን በሰብል ምርት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሆኗል። የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የጓሮ አትክልትና የእንስሳት እርባታ ሥራዎች ከፍተኛ ምርት የሚገኝባቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በርካታ የክፍለ ከተማችን ነዋሪዎችና ተቋማት የምግብ ፍጆታቸውን በራሳቸው በመሸፈንና ለገበያም በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ሁሉም ተግባሮቻችን ስኬታማ የሚሆኑት ሰላም ሲሰፍን ነው፣ ስለሆነም ክፍለ ከተማችን ብሎም ከተማችን አዲስ አበባ ሰላማዊ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፣ እያከናወነም ይገኛል። ክፍለ ከተማው በርካታ ሁነቶችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን የጸጥታ አካላትና የክፍለ ከተማችን የሰላም ሠራዊት በቅንጅት በመሆን ቀን ከሌት በትጋት እየሠሩ ይገኛሉ፣ በዚህም ልዩ ልዩ በዓላትና ሌሎች ሁነቶች በክፍለ ከተማችን በሰላም ተከናውነው ሊጠናቀቁ ችለዋል። ወንጀልን በመከላከልና ጸረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን በመቀልበስ ክፍለ ከተማችን ያከናወነው ስኬታማ ተግባር በመላው ሕዝባችን ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን። በአጠቃላይ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በሁሉም መስኮች የሚታይና የሚቆጠር ስኬታማ ተግባር ያከናወነና በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዚህ ስኬታችን አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ የክፍለ ከተማና የወረዳዎቻችን አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ተባባሪ አካላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የሰላም ሠራዊታችንና የጸጥታ አካላት በአጠቃላይ መላው የክፍለ ከተማችን ነዋሪዎች የእስከዛሬ አስተዋጽኦዋችሁን በማጠናከር ለጋራ ስኬታችን በጋራ ጥረታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል በክፍለ ከተማችን አስተዳደርና በራሴ ስም ጥሪዬን አቀርባለሁ።

እኛ እምንሰራው ?

1

የእኛ እይታ

የእኛ ተልእኮ ነዋሪዎቻችንን በትጋት፣ በቅንነት እና በፈጠራ ማገልገል ነው፣ ይህም ፍትሃዊ፣ የበለጸገ እና ለሁሉም ዘላቂ የሆነች ከተማ ለመፍጠር ነው።

2

የእኛ ተልዕኮ

ራዕያችን የሁሉንም ነዋሪ ህይወት የሚያበለጽግ እና ለሀገራችን ብልፅግና የሚያበረክተውን ደማቅ፣አካታች እና ዘላቂ የከተማ አካባቢን ማልማት ነው።

3

የእኛ እሴቶች

ራዕያችን ለሁሉም ነዋሪዎቿ የእድገት እና የብልጽግና ብርሃን ሆኖ የሚያገለግል ንቁ፣ አካታች እና ዘላቂ የከተማ አካባቢ መገንባት ነው።